የውኃና የለስላሳ መጠጥ አምራቾች ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተቃውሞ ደብዳቤ አቀረቡ

riporter

18 December 2019
ታምሩ ጽጌ
ኤክሳይዝ ታክስ በኢንቨስትመንትና በሠራተኞች ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ተሠግቷል

በሚኒስትሮች ምክር ቤት ፀድቆ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከቀረበ አንድ ሳምንት ያሳለፈውን የኤክሳይዝ ታክስ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ የተቃወሙ የውኃና ለስላሳ መጠጥ አምራቾች፣ ተቃውሞአቸውን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ለገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አቀረቡ፡፡
አምራቾቹ ተቃውሞአቸውን ያቀረቡት በኢትዮጵያ የታሸገ ውኃና ለስላሳ መጠጦች አምራች ኢንዱስትሪዎች ማኅበር አማካይነት ነው፡፡

የማኅበሩ ሊቀመንበር አቶ አሸናፊ መርዕድ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ውኃ እንደ ምግብ ስለሚቆጠር ኤክሳይዝ ታክስ ሊጣልበት አይገባም፡፡ በምግብ፣ በመድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን በአዋጅ ቁጥር 661/2002 እንደደነገገው፣ ውኃን ጨምሮ በምግብ ዘርፍ ላይ ኤክሳይዝ ታክስ አይጣልም ብለዋል፡፡
ነገር ግን ሰሞኑን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበውና ማክሰኞ ታኅሳስ 7 ቀን 2012 ዓ.ም. ለገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የተመራው ማሻሻያ ረቂቅ

አዋጅ፣ አምራች ኩባንያዎችን በከፍተኛ ሁኔታ የሚጎዳ ኤክሳይዝ ታክስ ለመጣል መዘጋጀቱ ተገቢ አለመሆኑን ሊቀመንበሩ ገልጸዋል፡፡ ለስላሳ መጠጦችም ቢሆኑ የተጋነነ ጭማሪ ሊጣልባቸው እንደማይገባም አክለዋል፡፡ ለስላሳ መጠጥ አምራቾች ከምርት ላይ 30 በመቶ ኤክሳይዝ ታክስ ይከፍሉ እንደነበር ያስታወሱት ሊቀመንበሩ፣ በረቂቅ ደረጃ በሚገኘው ኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ ላይ ግን ከሽያጭ 25 በመቶ እንዲከፍሉ መቅረቡን ተቃውመዋል፡፡ ይህ ማለትም ከምርት 30 በመቶ ይከፈል የነበረው የእርጅና ዋጋና የአስተዳደር ዋጋ ተቀናሽ ተደርጎ የነበረ ቢሆንም፣ ወደፊት ሊጣል በታሰበው 25 በመቶ ከሽያጭ ገቢ ማለት ያለ ምንም ተቀናሽ እንዳለ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ይህንን በምሳሌ ሲያስረዱ፣ አንድ ለስላሳ አምራች ድርጅት ከምርት 30 በመቶ ኤክሳይዝ ታክስ በሚከፈልበት ወቅት በዓመት ይከፍለው የነበረው ኤክሳይዝ ታክስ 100 ሚሊዮን ብር ቢሆን፣ በረቂቅ አዋጁ 25 በመቶ ከሽያጭ እንዲከፍል ሲደረግ በዓመት የሚከፍለው 175 ሚሊዮን ብር ይሆናል ብለዋል፡፡ ይህ ማለት ደግሞ በነበረው ላይ 75 በመቶ ከፍ እንደሚል አስረድተዋል፡፡

‹ማኅበሩ በዘርፉ አንቱ በተባሉ ኤክስፐርቶች ባስጣናው ጥናት እንዳረጋገጠው፣ መንግሥት እስካሁን ከምርት ያስከፍል የነበረው 30 በመቶ ተመዛዛኙ 14 በመቶ መሆኑ ተረጋግጧል፤›› ብለዋል፡፡ ነገር ግን ገንዘብ ሚኒስቴር ኤክሳይዝ ታክስ ለመጨመር ሳይሆን የታክስ መሠረቱን ለመቀየር መሆኑን ሲነግራቸው ሥሌቱን እንዴት እንደሠራው ሲጠየቅ፣ ‹‹ይህ የራሴ አሠራር ነው፣ ለአምራቾች አልገልጽም፤›› እንዳላቸውም አቶ አሸናፊ አስረድተዋል፡፡

በታሸገ ውኃ ከምርት ይከፈል የነበረው ኤክሳይዝ ታክስ 20 በመቶ እንደነበር የገለጹት ሊቀመንበሩ፣ በአዲሱ ረቂቅ ግን 15 በመቶ እንዲከፈል መደረጉን ገልጸዋል፡፡
ከላይ በለስላሳ መጠጦች ላይ እንደተባለው ሁሉ በአዋጅም እንደተረጋገጠው ውኃ እንደ ምግብ ስለሚቆጠር ኤክሳይዝ ታክስ ሊጣልበት የማይገባ ቢሆንም፣ ሲከፍል የነበረው 20 በመቶ ኤክሳይዝ ታክስ ተመዛዛኝ ሰባት በመቶ መሆኑን፣ ይህንንም በጥናት ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል፡፡ አሁን ከሽያጭ ላይ 15 በመቶ እንዲከፈል በረቂቅ መቅረቡ 50 በመቶ ጭማሪ መደረጉን እንደሚያሳይም አክለዋል፡፡

በታሸገ ውኃ ላይ ኤክሳይዝ ታክስ የምትጥለው ኢትዮጵያ ብቻ መሆኗን የጠቆሙት ሊቀመንበሩ ተመሳሳይ ምርት ያላቸው ደቡብ አፍሪካ፣ ኡጋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ አሜሪካ፣ ታይላንድና ሌሎች አገሮች ኤክሳይዝ ታክስ እንደማያስከፍሉ ተናግረዋል፡፡ ጎረቤት ኬንያ እንኳን አምስት በመቶ ብቻ የምትጥል መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም መንግሥት ውኃንና ለስላሳ መጠጦችን እንደ ቅንጦትና ጎጂ ነገሮች በማየት፣ ያረቀቀውን ኤክሳይዝ ታክስ ማሻሻያ አዋጅ እንደገና ሊመለከተውና ሊያስተካክለው እንደሚገባ፣ ለምክር ቤቱ ባስገቡት የመቃወሚያ ደብዳቤ ላይ አሳስበዋል፡፡ የሚመለከተው የመንግሥት አካልና ምክር ቤቱ የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ ያለ ምንም ማሻሻያ የሚያፀድቁት ከሆነ፣ በኢንቨስትመንትና በሠራተኞች ላይ ጉዳት ያስከትላል የሚል ሥጋት እንዳላቸውም አቶ አሸናፊ ተናግረዋል፡፡

በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶች ኢንቨስት ያደረጉት ሀብትና የያዙት ሠራተኛ፣ ከማንኛውም የኢንቨስትመንት መስክ የበለጠ ወይም የሚስተካከል መሆኑን ጠቁመው፣ የቀረበው አስፈሪ የኤክሳይዝ ታክስ ተግባራዊ ከሆነ ኢንቨስትመንቱ መዳከሙ የማይቀር መሆኑን ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡ ኤክሳይዝ ታክስ እንዳለ ቢጣል ድርጅቶቹ ለተጠቃሚ የሚያስተላልፉት መሆኑንና ተጠቃሚዎች አቅማቸው ካልቻለና ካልገዛቸው ደግሞ፣ ሥራውን እስከ ማቆም እንደሚደርሱም ያላቸውን ሥጋት ገልጸዋል፡፡ ይህ ደግሞ ሳይወዱ በግድ የቀጠሩትን ሠራተኛ መቀነስና ሲከፋም ሙሉ በሙሉ እስከ መዝጋት ሊያደርሳቸው እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ጊዜ በለስላሳ ምርቶቹ የሚታወቀው አንጋፋው ኢስት አፍሪካ ቦትሊንግ ኩባንያ በሰበታ አካባቢ በ300 ሚሊዮን ዶላር ለማስፋፋት ቦታ የወሰደ ቢሆንም፣ አሁን በተፈጠረው የኤክሳይዝ ታክስ ከፍተኛ ጭማሪ መደናገጥ ስለፈጠረበት በማመንታት ላይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በመሆኑም ምክር ቤቱ አምራች ድርጅቶቹ ከቋሚ ኮሚቴውና ከሚመለከታቸው መንግሥታዊ ተቋማት ባለሥልጣናት ጋር፣ በቀጣይ የሚያደርጉትን ውይይት አጽንኦት ሰጥቶ በመከታተል ተገቢ ውሳኔ እንዲያሳልፍላቸው አሳስበዋል፡፡ ማኅበሩ የለስላሳ ምርቶች ሰባት በመቶና የታሸጉ ውኃዎች ሁለት በመቶ (ሩብ ሊትር) ኤክሳይዝ ታክስ እንዲከፍሉና ሕዝቡ ጤንነቱ የተጠበቀ ውኃ በአራት ብርና ከዚያ በታች እንዲሸጥ ለማድረግ በመሥራት ላይ እንደነበርም አቶ አሸናፊ ተናግረዋል፡፡

 

Visitor Counter

Today 359

Yesterday 421

Week 2969

Month 2511

All 985471

Events - Calendar

October 2024
S M T W T F S
1 2 3 4 5
6 7 8 9 10 11 12
13 14 15 16 17 18 19
20 21 22 23 24 25 26
27 28 29 30 31

Contact Us

Office Phone: +251-116 663344

Mobile: +251-953855505

Fax: +251-116 663650

Email: info@ebmia.org

Website: www.ebmia.org

Addis Ababa, Ethiopia