- አትክልትና ፍራፍሬዎችን የሚያቀነባብሩ 16 ፋብሪካዎች ተዘግተዋል
የታሸጉ መጠጦችና የፍራፍሬ ጭማቂዎችን የሚያመርቱ ፋብሪካዎች ዘርፈ ብዙ ችግሮች ውስጥ እየገቡ መሆኑን እየገለጹ ነው፡፡ የኢትዮጵያ በቨሬጅስ አምራቾች ኢንዱስትሪዎች ማኅበር ባለፈው ሐሙስ ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ እንደተደመጠው በተለይ የታሸጉ ውኃዎች አምራቾችና የአትክልትና ፍራፍሬ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች ሥራቸውን ለማስቀጠል የሚያስችሉ የተለያዩ ተግዳሮቶች እየገጠማቸው ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት እየገጠሙ ያሉት ችግሮች በርካታ ናቸው ያሉት የማኅበሩ አባላት እየገጠሙን ላሉ ተግዳሮቶች መፍትሔ እየተገኘላቸው ባለመሆኑ ፋብሪካ እስከመዝጋት እየተደረሰ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ለዚህም ማሳያ የሚሆነው አትክልትና ፍራፍሬዎችን የሚያቀነባብሩ 16 ፋብሪካዎች ከሥራ ውጭ መሆናቸውን ለአብነት ገልጸዋል፡፡
የማኅበሩ ፕሬዚዳንት እንዳመለከቱት ጌትነት በላይ (ኢንጂነር) ለዘርፉ አባላት ስኬት ይረዳ ዘንድ ሰፋፊ ሥራዎችን እየሠራ ቢገኝም የተለያዩ ተግዳሮቶች ግን የዘርፉ አምራቾች ወደ ሚፈልጉት ደረጃ እንዳይደርሱ ገድቧቸዋል ያሉዋቸውን ምክንያቶች አቅርበዋል፡፡ በተለይ የጥሬ ዕቃ ከጊዜ ወደ ጊዜ መወደድ የኤክስይስ ታክስ ጫና፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ የኃይል መቆራረጥና የመሳሰሉት እየፈተኗቸው ስለመሆኑ በሪፖርታቸው ጠቅሰዋል፡፡ ለኮንሰንትሬት የሚሆን የሰኳር ግብዓት አለመኖር፣ የፖስት ኦዲት አሠራር ግልፅነት አለመኖር፣ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የተጣለው የጭነት ትራንስፖርት ዕገዳ እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ ችግሮች የበኩላችንን ድርሻ እንዳይወጡ ከማድረጋቸውም ባሻገር ይባስ ብሎ ኩባንያዎች እንዲዘጉ ምክንያት እስከመሆን ደርሷል ብለዋል፡፡ እይተፈጠሩ ባሉት ጫናዎች ምክንያት በተለይ አገር በቀል የአትክልትና ፍራፍሬ ማነባበሪያ ፋብሪካዎች ሙሉ ለሙሉ ሥራ ማቆማቸውን ተናግረዋል፡፡