የተፈጥሮ ውኃን በአግባቡ መጠቀም አስፈላጊነት ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው፡፡ አላቂ ሀብት ነው ተብሎ የሚታመነውን ውኃ በአግባቡና በቁጠባ መጠቀም ካልተቻለ ወደፊት እጥረት ይፈጠራል የሚል ሥጋትም አለ፡፡ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የውኃ ሀብት አላት ቢባልም፣ በአግባቡ መጠቀም ካልተቻለ የችግሩ ሰላባ ትሆናለች የሚሉ ምልከታዎች እየተንፀባረቁ ነው፡፡ በከፍተኛ ደረጃ ውኃን ዋነኛ ግብዓት አድርገው የሚጠቀሙ ፋብሪካዎች የውኃ እጥረት የሚያጋጥማቸው ወቅት አለ፡፡ ይህ ጉዳይ ዝም ከተባለና ውኃን ቆጥቦ በመጠቀም በጋራም ሆነ በግል መሥራት ካልተቻለ፣ እ.ኤ.አ. በ2030 የውኃ እጥረት ሊያጋጥም ይችላል የሚል በጥናት ላይ የተመሠረተ ትንታኔ ይቀርባል፡፡