የታሸጉ መጠጦችና የፍራፍሬ ጭማቂ አምራቾች በኤክሳይዝ ታክስና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ቅሬታ አቀረቡ
የኢትዮጵያ በቬሬጅስ አምራቾች ኢንዱስትሪዎች ማኅበር ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔውን ባካሄደበት ወቅት
Featured

የታሸጉ መጠጦችና የፍራፍሬ ጭማቂ አምራቾች በኤክሳይዝ ታክስና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ቅሬታ አቀረቡ

  • አትክልትና ፍራፍሬዎችን የሚያቀነባብሩ 16 ፋብሪካዎች ተዘግተዋል

የታሸጉ መጠጦችና የፍራፍሬ ጭማቂዎችን የሚያመርቱ ፋብሪካዎች ዘርፈ ብዙ ችግሮች ውስጥ እየገቡ መሆኑን እየገለጹ ነው፡፡ የኢትዮጵያ በቨሬጅስ አምራቾች ኢንዱስትሪዎች ማኅበር ባለፈው ሐሙስ ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ እንደተደመጠው በተለይ የታሸጉ ውኃዎች አምራቾችና የአትክልትና ፍራፍሬ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች ሥራቸውን ለማስቀጠል የሚያስችሉ የተለያዩ ተግዳሮቶች እየገጠማቸው ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት እየገጠሙ ያሉት ችግሮች በርካታ ናቸው ያሉት የማኅበሩ አባላት እየገጠሙን ላሉ ተግዳሮቶች መፍትሔ እየተገኘላቸው ባለመሆኑ ፋብሪካ እስከመዝጋት እየተደረሰ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ለዚህም ማሳያ የሚሆነው አትክልትና ፍራፍሬዎችን የሚያቀነባብሩ 16 ፋብሪካዎች ከሥራ ውጭ መሆናቸውን ለአብነት ገልጸዋል፡፡

የማኅበሩ ፕሬዚዳንት እንዳመለከቱት ጌትነት በላይ (ኢንጂነር) ለዘርፉ አባላት ስኬት ይረዳ ዘንድ ሰፋፊ ሥራዎችን እየሠራ ቢገኝም የተለያዩ ተግዳሮቶች ግን የዘርፉ አምራቾች ወደ ሚፈልጉት ደረጃ እንዳይደርሱ ገድቧቸዋል ያሉዋቸውን ምክንያቶች አቅርበዋል፡፡ በተለይ የጥሬ ዕቃ ከጊዜ ወደ ጊዜ መወደድ  የኤክስይስ ታክስ ጫና፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ የኃይል መቆራረጥና የመሳሰሉት እየፈተኗቸው ስለመሆኑ በሪፖርታቸው ጠቅሰዋል፡፡ ለኮንሰንትሬት የሚሆን የሰኳር ግብዓት አለመኖር፣ የፖስት ኦዲት አሠራር ግልፅነት አለመኖር፣ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የተጣለው የጭነት ትራንስፖርት ዕገዳ እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ ችግሮች የበኩላችንን ድርሻ እንዳይወጡ ከማድረጋቸውም ባሻገር ይባስ ብሎ ኩባንያዎች እንዲዘጉ ምክንያት እስከመሆን ደርሷል ብለዋል፡፡ እይተፈጠሩ ባሉት ጫናዎች ምክንያት በተለይ አገር በቀል የአትክልትና ፍራፍሬ ማነባበሪያ ፋብሪካዎች ሙሉ ለሙሉ ሥራ ማቆማቸውን ተናግረዋል፡፡ 

ዘርፉ ላይ አግባብነት የሌለው ኤክሳይዝ ታክስ መጣሉ ሌላው ችግር እንደሆነ ከተሰጠው ማብራሪያ መረዳት ተችሏል። በአሁኑ ሰዓት በታሸጉ ውኃ አምራቾች፣ የለስላሳ አምራቾች እንዲሁም በቅርቡ ደግሞ በአትክልትና ፍራፍሬ አቀናባሪዎች (ጁስ አምራቾች) ላይ የተጣለውን ኤክሳይስ ለሥራቸው እንቅፋት ሆኗል ይላሉ፡፡ ይህም በመሆኑ ማኅበሩ በነዚህ ምርቶች ላይ የተጣለው ኤክሳይዝ ታክስ ታክስ ሙሉ በሙሉ እንዲነሳ በማድረግ አስፈላጊውን መረጃ በባለሙያ አስጠንቶ ለገንዘብ ሚኒስቴርና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በማቅረብ አዎንታዊ ምላሽ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማግኘት እየተሞከረ ስለመሆኑ አስታውቀዋል፡፡  

ለፋብሪካዎቹ መዘጋት በዋናነት የሚጠቀሰው ክፈሉ የተባሉት ኤሳይዝ ታክስና በገበያ ውስጥ ለመወዳደር የሚያስችላቸው አቅም በማጣታቸው ጭምር መሆኑን የገለጹት የማኅበሩ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አሸናፊ መርድ በተለይ የአገር ውስጥ የአትክልትና ፍራፍሬ ማቀነባበሪያዎች ከእነዚህ ችግሮች ጋር በተያያዘ 16 ፋብሪካዎች ሥራ አቁመው ሠራተኞች መበተናቸውን አክለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ወደ 26 የሚሆኑ የአትክልትና ፍራፍሬ አምራቾች ያሉ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 16ቱ አገር በቀል ኩባንያዎች ናቸው ያሉት አቶ አሸናፊ እነዚህ ኩባንያዎች ከኤክሳይስ ታክሱ ጫና ባሻገር ጥሬ ዕቃ ለማግኘት ያለባቸው የውጭ ምንዛሪ እጥረትም ችግር ስለሆነባቸው ተወዳዳሪ ለመሆን ባለመቻላቸው ፋብሪካዎቻቸውን እስከመዝጋት ደርሰዋል፡፡ 

 በተለይ ከ2012 ዓ.ም. ጀምሮ በወጣው አዋጅ መሠረት እነዚህ የአትክልትና ፍራፍሬ አቀነባባሪዎች ኤክሳይዝ ታክስ ክፈሉ ከመባላቸው ጋር ተያይዞ የገጠማቸው ችግር ታክሱን ወደ ኋላ ተመልሰው እንዲከፍሉ ጭምር የተጠየቁ በመሆኑ ይህንን የመክፈል አቅም ማጣታቸው ሥራውን ለማስቀጠል አላስቻላቸውም፡፡

ይህንን ችግር ለመፍታት ማኅበሩ ይመለከታቸዋል ከተባሉ መንግሥታዊ ተቋማት ጋር እየተነጋገረ ሲሆን፣ እንደ መፍትሔ ቢያንስ ወደ ኋላ ተመልሶ ኤሳይዝ ታክስ ክፍሉ የሚለው እንዲቀር ለማድረግ ጥረት እያደረገ ስለመሆኑ ከተሰጠው ማብራሪያ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ 

እንዲህ ባሉ ምክንያቶች ከገበያ የወጡት የአገር ውስጥ አምራቾች በተመሳሳይ ዘርፍ የሚሠሩ ወደ ሰባት የሚደርሱ የቻይና ኩባንያዎች ግን ገበያውን እንዲቆጣጠሩ ማድረጉም ተገልጿል፡፡ 

እነዚህ የቻይና ፋብሪካዎች የጥሬ አቅርቦትና የውጭ ምንዛሪ ችግር ስለሌለባቸው ገበያውን መቆጣጠራቸውን የአገር ውስጥ አምራቾች በሩ ዝግ እንዲሆን እንዳደረገ  ተጠቅሷል፡፡ 

ኤክሳይስ ታክስ ከዚህ ቀደም በታሸጉ ውኃ አምራቾች ላይ (የአሥር በመቶ) ከሽያጭ የተጣለ መሆኑን የሚያመለክተው የማኅበሩ መረጃ ይህ የታክስ መጠን እንዲቀንስ ወይም እንዲነሳ በተደጋጋሚ ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ቢቀርብም ምላሽ ባያገኝም አሁንም ምላሽ ለማግኘት ጥረት እየተደረገ ስለመሆኑ ሥራ አስኪያጁ አስታውቀዋል፡፡ ከዚህ ከታክስ ጋር በተያያዘ  በሁሉም ክልሎች በተመሳሳይ ሀኔታ ኤክሳይስ ታክስ ተግባራዊ አለመደረጉንና ይኸው ደግሞ በአምራቾች ላይ አላስፈላጊ ውድድር እየፈጠረ መሆኑ ለቀረበ ጥያቄ ግን አዎንታዊ ምላሽ መገኘቱን አመልክተዋል፡፡ ይህም የገንዘብ ሚኒስቴር በቅርቡ የኤክሳይስ ስታምፕ በፌዴራልና በሁሉም ክልሎች በተመሳሳይ ሁኔታ ተግባራዊ ለማድረግ መወሰኑ በአዎንታዊ መልኩ የሚታይ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ የአትክልትና ፍራፍሬ አቀናባሪዎችና አምራቾች በኩልም ደግሞ ልክ እንደ ውኃ ሴክተሩ ኤክሳይስ ታክስ በቅርቡ የተጣለበት ሲሆን፣ እንዲጣልበት በመደረጉ ተፈጠረ የተባለውን ችግር ለመቅረፍ ማኅበሩ የተለያዩ አማራጮችን በመውሰድ ችግሩ እንዲፈታ ጥረት እያደረገ ሲሆን ሌሎች ችግሮችም እንዲፈቱ በተለያዩ መንገዶች ውይይት እየተደረገ ነው ተብሏል፡፡ በተለይ የፍራፍሬ ጭማቂ ደረጃን በተመለከተ እንዲደረግ የሚፈለገውን ማስተካከያ በማስጠናት ለሚመለከተው ክፍል ማቅረባቸው በምሳሌነት ተጠቅሷል፡፡

በአሁኑ ወቅት ወደ 26 የሚሆኑ የአትክልትና ፍራፍሬ አምራቾች ያሉ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 16ቱ አገር በቀል ኩባንያዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ኩባንያዎች ከኤክሳይዝ ታክስ ጫና ባሻገር ጥሬ ዕቃ ለማግኘት ያለባቸው የውጭ ምንዛሪ እጥረትም ችግር ስለሆነባቸው ተወዳዳሪ ለመሆን ባለመቻላቸው ፋብሪካዎቻቸውን ዘግተው ሠራተኞች እስከመበተን መድረሳቸውን አቶ አሸናፊ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በተለይ ከ2012 ዓ.ም. ጀምሮ በወጣው አዋጅ መሠረት እነዚህ የአትክልትና ፍራፍሬ አቀነባባሪዎች ኤክሳይዝ ታክስ ክፈሉ መባላቸው ጋር ተያይዞ የገጠማቸው ችግር ታክሱን ወደ ኋላ ተመልሰው እንዲከፍሉ ጭምር የተጠየቀ በመሆኑ ይህንን የመክፈል አቅም ማጣታቸው ሥራውን ለማስቀጠል አላስቻላቸውም፡፡

ይህንን ችግር ለመፍታት ማኅበሩ ይመለከታቸዋል ከተባሉ መንግሥታዊ ተቋማት ጋር እየተነጋገረ ሲሆን፣ እንደ መፍትሔ ቢያንስ ወደ ኋላ ተመልሶ ኤክሳይዝ ታክስ ክፍሉ የሚለው እንዲቀር ለማድረግ ጥረት እያደረገ ስለመሆኑ ከተሰጠው ማብራሪያ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡

እንዲህ ባሉ ምክንያቶች ከገበያ የወጡት የአገር ውስጥ አምራቾች ገበያውን በተመሳሳይ ዘርፍ የሚሠሩ ወደ ሰባት የሚደርሱ የቻይና ኩባንያዎች እንዲያዩት ምክንያት መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

እነዚህ የቻይና ፋብሪካዎች የጥሬ አቅርቦትና የውጭ ምንዛሪ ችግር ስለሌለባቸው ገበያውን መቆጣጠራቸውን የአገር ውስጥ አምራቾች በሩ ዝግ እንዲሆን እያደረገ ስለመሆኑም ተጠቅሷል፡፡ 

ሌላው የዘርፉ ዋነኛ ችግር ሆኗል ተብሎ በዕለቱ በተገኙ የጠቅላላ ጉባዔ አባላት የተነሳው የታሸጉ ውኃዎች የገጠማቸው የገበያ ችግር ነው። የውኃ አምራቾች የገበያ ችግር ሥር እየሰደደ መሆኑንና ለዚህ ችግር አንዱ ምክንያት የፀጥታ ችግር ነው ተብሏል፡፡ ይህንኑ ችግር ለመቀረፍ የተወሰኑት የዘርፉ አምራቾች ገንዘብ በማዋጣት ሕዝቡ የታሸገ ውኃ መግዛት እንዲችል በማስታወቂያ እንዲነገር ሰፊ ሥራ የተሠራ ቢሆንም ሕዝቡ የታሸገ ውኃ እንዲጠጣ ሌሎች ተጓዳኝ ፕሮግራሞችን በመቅረፅ በመሥራት ላይ እንደሚገኙም ማብራሪያ ተሰጥቶበታል፡፡ 

‹‹የገበያ ዕጦቱ አንዱና ዋነኛ ምክንያቱ የፀጥታ ችግር ነው፡፡ እንደ ልብ መንቀሳቀስ አልተቻለም ስለዚህ ብዙዎቹ የውኃ አምራቾች ሽያጫቸው በከተማ ብቻ እንዲገደብ አድርጓል፤›› ያሉት አቶ አሸናፊ ገበያቸው ላይ ተፅዕኖ ፈጥሯል፡፡ 

ወደ አንዳንድ የክልል ከተሞች ምርቶቻቸውን ማድረስ ባለመቻላቸውም በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ 52 የታሸጉ የውኃ ዓይነቶች ገብተው እንዲሸጡ አስገድዷል፡፡ ይህ ደግሞ ከፍላጎት በላይ ምርቱ እንዲቀርብ በሚደረጉ ብዙዎች የገበያ ዕጦት እንዲገጥማቸው አድርጓል በማለት ችግሩን አስረድተዋል፡፡ 

አምራቾቹ የጥሬ ዕቃና የፋይናንስ አቅርቦት ችግር ሌላው የዚህ ዘርፍ ማነቆ ሆኖ የተጠቀሰ ሲሆን፣ የጉምሩክ አሠራር ችግርም እንዳልተፈታ ተገልጿል፡፡ ከገቢዎች ጋር በተያየዘ ከየፖስት ኦዲት ጋር በተያያዘ አሉብን ያሉትን ችግር አባላቱ የገለጹ ሲሆን፣ የኃይል መቆራረጥ የውጭ ምንዛሪ ችግርና ሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮች ለሥራቸው እንቅፋት ሆኗል፡፡ በነዚህ ጉዳዮች ላይ ማኅበሩ ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጋር በመሆን በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ዕቅድ ውስጥ ተካቶ መፍትሔ እንዲያገኝ በመሥራት ላይ የሚገኝ ሲሆን የተገኘው ውጤት ግን በቂ አለመሆኑን አሳውቋል፡፡   

ከዚህም ሌላ በተለይ የውኃ አምራቾች አሳሳቢ ሆኖብናል ብለው በጠቅላላ ጉባዔው ያስታወቁት በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ የታሸገ ውኃ አምራቾች የውኃ ፈንድ በሚል ከዓመታዊ ሽያጫቸው ላይ አንድ በመቶ እንዲከፍሉ እይተጠየቁ መሆኑ ነው፡፡

ይህ በክልሉ መንግሥት ተወስዶ ይተገበራል የተባለው የውኃ ፈንድ ከጥቅል ሽያጫቸው አንድ በመቶ እንዲከፍሉ የሚያስገድድ ነው፡፡ ለውኃ ፈንድ ከሽያጭ ላይ የሚሰበሰበው ገንዘብ መጠን እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ በዚህ ሥሌት መክፈል የማይቻል እንደሆነ የውኃ አምራቹ ገልጸዋል፡፡ በጠቅላላ ጉበዔው ላይም ይህ ጉዳይ መፍትሔ ሊፈለግለት ካልተገባ በቀር ውሳኔውን ተግባራዊ ማድረግ አስቸጋሪ እንደሚሆን ሁሉ ገልጸዋል፡፡

አሁን ላይ በግድ መክፈል ይጠበቅባቸዋል እየተባሉ መሆኑ እንዳሳሰባቸው አምራቾቹ የገለጹ ሲሆን፣ ማኅበሩም ከሚመለከተው የኦሮሚያ ክልልና ከሸገር ሲቲ ከተማ አስተዳደር ጋር እንደሚነጋገርበት አስታውቀዋል፡፡

የውኃ ፈንድ እንዲከፈል የሚለው አግባብ ሊሆን ቢችልም ፈንዱ የሚሰበሰበው ከሽያጭ ላይ ይሁን መባሉ ተገቢ ሊሆን እንደማይችል ያመለከቱት ፕሬዚዳንቱ ደግሞ ማኅበራቸው እንደ መፍትሔ ያቀረበው የውኃ ፈንዱ ክፍያ ከተጣራ ትርፍ ላይ ታሳቢ እንዲሆን የሚል በመሆኑ ይህንኑ ጥያቄ በማቅረብ እንዲስተካከል ጥያቄያቸውን የሚገፋ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ከጠቅላላ ሽያጭ ላይ ይታሰብ ከተባለ ግን ከውኃ አምራቹ አቅም በላይ ስለሚሆን ችግር ሊያስከትልባቸው እንደሚችልም ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

ክልሉ በወሰነው ውሳኔ መሠረት የውኃ ፈንዱ ከሽያጭ ላይ እንደሚሰበሰብ ያስታወቀ በመሆኑና ይህንን ተፈጻሚ ማድረግ ያልቻሉ የታሸገ ውኃ አምራቾች ሥራቸውን ሊቀጥሉ እንዳይችሉ ሊዳረጉ ይችላሉ ተብሎ እየተገለጸላቸው በመሆኑ ሁኔታው እንዳሳሰባቸውም ገልጸዋል፡፡

አቶ አሸናፊ በበኩላቸው ይህ ጉዳይ ያሳስባል ክልሉ በወሰነው ውሳኔ መሠረት ከሽያጭ ለውኃ ፈንዱ ገቢ ካልተደረገ ፈቃድ አናድስም ከተባለ ነገሩን አስቸጋሪ ስለሚያደርገው ውሳኔው ከመተግበሩ በፊት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሁሉ እንነጋገርበታል ብለዋል፡፡ እንዲህ ላሉ ችግሮች መፍትሔ ካልተበጀ እንደ አትክልትና ፍራፍሬ ማቀነባበሪያዎቹ የውኃ አምራቾቹም ተመሳሳይ ዕጣ እንዳይገጥማቸው ይሠጋሉ፡፡ በመሆም ችግሮቻችን ታይተው መፍትሔ እንሻለን ያሉት የማኅበሩ አባላት ትኩረት ሊሰጠን ይገባል ብለዋል፡፡ 

የማኅበሩ ፕሬዚዳንትም አገራችን ከግብርና ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪው መር በምታደርገው ሽግግር የአምራቹን ዘርፍ ሁለንተናዊ አቅም መገንባት ብሎም ለአገራቸን ዕድገት ዕውን መሆን የአምራቹ ሚና በተለይም የዚህ ዘርፍ ሚና መተኪያ የሌለው እንደሆነ የገለጹት የማኅበሩ ቦርድ ሰብሳቢ መንግሥትና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ለዚህ ዘርፍ ዕድገት የበኩላቸውን ድጋፍ ሊያደርጉለት ይገባል ብለዋል፡፡ 

Source : https://www.ethiopianreporter.com/129679/

Visitor Counter

Today 279

Yesterday 421

Week 2889

Month 2431

All 985391

Events - Calendar

October 2024
S M T W T F S
1 2 3 4 5
6 7 8 9 10 11 12
13 14 15 16 17 18 19
20 21 22 23 24 25 26
27 28 29 30 31

Contact Us

Office Phone: +251-116 663344

Mobile: +251-953855505

Fax: +251-116 663650

Email: info@ebmia.org

Website: www.ebmia.org

Addis Ababa, Ethiopia